የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ግንቦት 28 ቀን 2017 ዓ.ም
መንግስት ያስተላለፈውን የሰላም ጥሪ በመቀበል ከነ ሙሉ ትጥቃቸው እጃቸውን የሰጡት 12 በሰሜን ጎጃም ጫካ ገብተው የነበሩ አመራሮች ናቸው።
እጅ በሰጠው ቡድን ስር በራሱ አደረጃጀት እራሱን የኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህ ብርጌድ ብሎ ከሚጠራው መካከል
1. ሻምበል መንግስቱ ድልነሳ አለም – ሻለቃ አዛዥ
2. መቶ አለቃ ምስጋናው ሽታ ገረመው – ሻለቃ ዘመቻ ሀላፊ
3. ዶክተር አንለይ አሰፋ ዘላለም – በአቸፈር ቀጠና አቤ ጎበኛ ብርጌድ አስተዳደር እና ጸጥታ ሀላፊ እና ሌሎች ስምንት አመራሮች እና አባላቱ መንግሰት የሰጣቸውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው እጅ ሰጥተዋል።
በሰላም እጅ ሲሰጡ የሰሜን ጎጃም ዞን ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ሀላፊ አቶ ገብረስላሴ ታዘብ፣ የምስራቅ ዕዝ አንድ ኮር አመራሮች ፣ የመርዓዊ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ብርሃኑ አበረ፣ የመርዓዊ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታነህ መልኬ ተገኝተዋል።
እጅ ከሰጡት መሐል አንዳንዶቹ እንደተናገሩት ፣ እስካሁን የሄድንበት የተሳሳተ መንገድ በመሆኑ እኛም፣ ቤተሰቦቻችንም እና መላ ህዝባችንም ብዙ ዋጋ ከፍለናል፤ ብዙ ወንደሞቻችን እና እህቶቻችን አጥተናል፤ ተጨማሪ ህይወት መጥፋት የለበትም፤ ነገ ድርድር ቢደረግ የማናገኛቸውን ወጣቶች ማጣት የለብንም ብለን የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለን የህዝባችንን መከራ ለማቆም ወስነን እጅ ሰጥተናል ብለዋል።
አሁንም በተሳሳተ መንገድ ላይ ያሉ ወንድሞቻችን የእኛን ፈለግ ተከትለው መንግስት የዘረጋው የሰላም እጅ ሳይታጠፍ ህይወታቸውን ለቤተሰቦቻቸው እንዲያቆዩ ወንድማዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን ብለዋል።
በተያያዘ ዜና በአዴት ዙሪያ በዴንሳባታና በአጊታ ቀበሌ የተሰማራው በምስራቅ ዕዝ ስር የሚገኝ አንድ ሬጅመንት በፅንፈኛው ቡድን ላይ በወሰደዉ እርምጃ አስር የጠላት ሀይል ሲደመስስ አንድ መትረየሰ ማርኳል፡፡
የዕዙ የሠራዊት አባላት በተሰማሩባቸዉ የግዳጅ ቀጠናዎች የሰላምን አማራጭ ባልተቀበሉ የፅንፈኛው ቡድን ላይ እግር በእግር እየተከታሉ የመደምሰሱን ተግባር አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡
ሰሞኑን በአዴት ዙሪያ በዴንሳባታና በአጊታ ቀበሌ ከጠላት ጋር የተደረገዉን ኦፕሬሽን አስመልክተው የአንድ ሬጅመንት አዛዥ ሻለቃ ባሻ ፈንታሁን አሰፋ እንደተናገሩት፣ በነበረን ስምሪት ጠላትን ከገባበት ገብቶ በማሳደድ ጠንካራ ምት አሳርፈንበታል፤ በዚህም ዘመቻ አስር የጠላት ሀይል በመደምሰስ 12 በማቁሰል ፣ አንድ ፒ ኬ ኤም/መትረየስ ፣ አንድ ባለ 100 የመትረየስ ሸንሸል፣ ሁለት ክላሽ ፣ ሁለት ካዝና ፣ ሰባት ቃታ መሳሪያ ፣ አንድ የስናይፐር መነፅር እና 187 ተተኳሽ ጥይት ማርከናል ብለዋል፡፡
በተሰለፍንበት የግዳጅ ቀጠና የአካባቢዉ ህብረተሰብ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ እና ወደ መሰረተ ልማት የበለጠ ትኩረቱን አድርጎ እንዲሰራ የምናደርገዉን የጠላት ሀይል ለይቶ የመደምሰስ ግዳጃችንን ከአካባቢዉ ህብረተሰብና የፀጥታ አካላት ጋር አቀናጅተን እንቀጥላለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ ታደሰ ይሴ
ፎቶግራፍ ከሬጅመንት
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ድረ-ገፅ
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ዩቲዩብ
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ቴሌግራም
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ፌስቡክ