የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ በወታደራዊ ሳይንስ፣ በስነ-ምግባር፣ በትጋት እና በሃገር ፍቅር ጥግ ያሰለጠናቸውን የ71ኛ መተማ ኮርስ ዕጩ መኮንኖች በዛሬው ዕለት በደማቅ ስነ-ስርዓት አስመርቋል።
የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ጌታቸው ሃብታሙ፤ ጀግንነት በጦር ሜዳ መዋጋት ብቻ ሳይሆን ለእውነት፣ ለፍትህና ለሰላም ጸንቶ መቆም፣ ህዝብን በቅንነት ማገልገልና ሀገርን መወደድ ጭምር መሆኑን በምረቃ መርሃ-ግብሩ አሥገንዝበዋል።

ተመራቂዎቹ የተቀበሉትን የወታደራዊ አመራር ማዕረግና እውቀት ተጠቅመው የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና ደህንነት በጽናት መጠበቅ እንደሚጠበቅባቸውም አሥገንዝበዋል።
ብርጋዲየር ጄኔራል ጌታቸው ሀብታሙ እንደገለጹት፤ ተመራቂዎቹ በቆይታቸው አካላዊ፣ አእምሯዊና ስነ-ልቦናዊ ፈተናዎችን አልፈው የላቀ የጦር አመራር ክህሎትን ተላብሰዋል።
ትምህርቱም በንድፈ-ሀሳብና በጠንካራ የመስክ ልምምዶች የተደገፈ በመሆኑ፣ አዲሶቹ መኮንኖች በማንኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ሀገራዊ ግዴታቸውን በብቃት የመወጣት ሙሉ ዝግጅትና ቁርጠኝነት እንዳላቸው አረጋግጠዋል።

አካዳሚው የተሰጠውን ሀገራዊና ተቋማዊ ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት የዘመኑን የቴክኖሎጂና የእውቀት እድገት ያገናዘቡ የትምህርትና የስልጠና ማሻሻያዎችን እያደረገ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በሳይንሳዊ ጥናቶች ላይ በመመስረት የካዴት ትምህርቱን ደረጃ ከማሳደግ ባለፈ፣ የከፍተኛ አመራሮችንና ባለሙያዎችን አቅም የሚያጎለብቱ የሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት ፕሮግራሞችን ለመጀመር ዝግጅት መጠናቀቁን የአካዳሚው አዛዥ ጠቁመዋል።
ከዋናው የትምህርትና ስልጠና ተልዕኮ ጎን ለጎን፣ አካዳሚው የአካባቢውን ደህንነት ከመጠበቅ ባሻገር በግብርና፣ በእንስሳት እርባታና በራስ አቅም የመሰረተ-ልማት ግንባታ በርካታ የአካባቢ ልማት ስራዎችን በማከናወን ረገድ አርአያነት ያለው ሰፊ እንቅስቃሴ አድርጓል ያሉት ብርጋዲየር ጄኔራል ጌታቸው ሀብታሙ ይህም ተቋሙ የወታደራዊ ትምህርት ማዕከል ብቻ ሳይሆን የማህበረሰብና የልማት አጋር መሆኑን ዳግም በተግባር ያረጋገጠበት እንደሆነ አብራርተዋል።

በመጨረሻም ብርጋዲየር ጄኔራል ጌታቸው ሃብታሙ ተመራቂዎች ላለፉት ሦስት ዓመታት የነበራቸውን የጽናትና የትጋት ጉዞ በማድነቅ ለመላው ተመራቂዎችና ለቤተሰቦቻቸው የእንኳን ደስያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ አብርሃም ዘርጋው
ፎቶግራፍ ፉራ አብደላ
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ድረ-ገፅ
https://dfmc.mod.gov.et/
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ዩቲዩብ
https://youtube.com/@fdredefenseforce-9629?si=Av-sDKCopw1FfTW2
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ቴሌግራም
https://t.me/+E_EOiTY9eq85ODI0
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ፌስቡክ
https://www.facebook.com/fdredefense.official
