በደቡብ ሱዳን ደቡባዊ ሴክተር ተሰማርቶ የሚገኘው የ22ኛ ሞተራይዝድ ሰላም አስከባሪ ሻለቃ የተሰጠውን ተልዕኮ በላቀ ብቃት በመወጣት ውጤት እያስመዘገበ እንደሚገኝ ተገለፀ፡፡
የኢትዮጵያ ሠራዊት በማንኛውም ዓይነት ተግዳሮትና ፈታኝ ሁኔታ ሳይረታ የሚሰጠውን ተልዕኮ በብቃት መፈጸም የሚችል ጀግና መሆኑን በደቡብ ሱዳን የደቡብ ሴክተር ዋና አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ሺሺር ባራድዋጅ ገለፁ።

ዋና አዛዡ በቀጠናው ተሰማርቶ ለሚገኘው የ22ኛ ሞተራይዝድ ሠላም አሥከባሪ ሻለቃ አመራር እና አባላት በቀጠናው በተሰማሩ አጭር ጊዜ ውስጥ ላስመዘገቡት እና እያስመዘገቡ ላለው ውጤታማ የተልዕኮ አፈጻጸም ምስጋናና ዕውቅና በመስጠት የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ሠራዊት ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎችን በስኬት የመወጣት የረጅም ጊዜ ታሪክ እና ልምድ ያለው መሆኑን ያወሱት ጄነራል መኮንኑ አሁን ላይ የሻለቃው አባላት በደቡብ ሱዳን እያሳዩት ያለው ጀግንነትና የዲሲፕሊን ልዕልና የአገሪቱን መልካም ስም ይበልጥ የሚያስጠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ በፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ የታየው ቁርጠኝነት ለአካባቢው ማህበረሰብ አስተማማኝ ዋስትና የሚሰጥ እና ለቀጣይ የሰላም ጥረቶች ትልቅ መነሳሳትን የሚፈጥር መሆኑን በመገንዘብ ሠላም አስከባሪዎች የተጣለባቸውን አለም አቀፋዊ ኃላፊነት በታማኝነትና በጀግንነት ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የሞተራይዝድ ሻለቃው በቀጠናው በተሰማራ በአጭር ጊዜ ውስጥ እያስመዘገበ ላለው ውጤታማ የተልዕኮ አፈጻጸም ያላቸውን ከፍተኛ አድናቆት በመግለጽ ለሻለቃው አመራር እና አባላት የዕውቅና ሰርተፊኬት አበርክተዋል።
ዘጋቢ ቢኒያም ማሞ
ፎቶ ግራፍ ገዛኸኝ ፀጋዬ
