ኢትዮጵያ በየዘመኑ በታሪካዊ ጠላቶች እና በውስጥ ባንዳዎች ብትፈተንም፤ ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት የእነኝህን ኃይሎች ፍላጎት እያከሸፈው ይገኛል ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ክቡር ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለፁ።
በኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ የ71ኛ ዙር መተማ ኮርስ ካዴት ዕጩ መኮንኖች ምርቃት ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ቀጠና የምትገኘው ኢትዮጵያ በታሪካዊ ጠላቶች በየዘመኑ ስትፈተን መቆየቷን አውስተው፤ በታሪካዊ ጣላቶች እና በባንዳዎች የተሰራው የክፍት ደባ ጉዳት አላደረሰም ባይባልም ጀግናው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ይህን እኩይ የጥፋት ሴራ በጀግንነት እያከሸፈ ይገኛል ብለዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ኢትዮጵያም ፈተና ቢበዛባትም፤ ፈተናውን በጀግኖች ልጆቿ እያለፈች ትገኛለችም ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ ተመራቂዎችም ይህን አኩሪ ተጋድሎ ለማስቀጠል ለእናት ሃገራቸው በየዘመኑ መስዋዕትነት እየከፈሉ ይገኛሉ ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አካዳሚው ኢትዮጵያን ያስቀጠሉ ጀግኖች መኮንኖችን ያፈራ የወታደራዊ የልህቀት ማዕከል እንደሆነም አብራርተዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አካዳሚው የስርዓተ ትምህርቱን ዘመኑ በሚጠይቀው እውቀት በማዘመን፣ በማሻሻል ለተቋማዊ ፕሮፌሽናሊዝም ምቹ መደላደል የፈጠረ አንጋፍ አካዳሚ ሥለመሆኑም ገልፀዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተመራቂ ዕጩ መኮንኖች ያሳዩትን ተነሳሽነት አድንቀው፤ በስልጠናው ያገኙት እውቀት የሚዳብረው በሚቀለቀሉበት የጦር ክፍል በተግባር በሚያገኙት ልምድ እና እውቀት ሥለሆነ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

ዘጋቢ አብርሃም ዘርጋው
ፎቶግራፍ ፉራ አብደላ
