ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
የኢፌድሪ መከላከያ ሠራዊት ግንቦት 30 ቀን 2017 ዓ.ም.
መከላከያ ሠራዊቱ በየጊዜው የሚፈጠሩ ውስብስብ ፈተናዎችን እያሸነፈና በፅናት እያለፈ የሀገሩን ሉዓላዊነት አስከብሮ አስቀጥሏል ሲሉ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ተናገሩ።
የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል ያሰለጠናቸውን የ43ኛ ዙር ካራማራ ኮርስ መሰረታዊ ኮማንዶዎችን ሲያስመርቅ በክብር እንግድነት የተገኙት የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ኢትዮጵያ በአይበገሬ ጀግኖች ልጆቿ የሚያጋጥሟትን ፈተናዎች በፅናት በመታገል የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፈው የሚሰጡ የሀገር ባንዳዎችን በመመከት ከዘመን ዘመን መሻገሯን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያን የውስጥና የውጭ ፀረሰላም ሀይሎች ተናበው ብሄራዊ ጥቅሟን ለመጉዳትና ሉዓላዊነቷን ለመዳፈር በየዘመናቱ የሚደረጉ ሙከራዎችን ሠራዊቱ የህይወትና የአካል መስዋዕትነት ከፍሎ ማሸነፉንም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በትጥቅም ይሁን በአደረጃጀት አስተማማኝ የመከላከያ ሠራዊት መገንባቷን ያነሱት ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ይህም በቀጣይነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስተዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ማሰልጠኛም የሐገርና የሕዝብ ኩራት የሆነ ቀጣይ ለሚሰጠው ተልዕኮ ሳይንሳዊ በሆነ የአሰለጣጠን ዘዴ በመጠቀም በአጭር ኪሳራ በጠላት ላይ ድልን የሚቀዳጅ ሠራዊት ማፍራቱን መመልከታቸውን ጠቁመው ሰልጣኛችም የተሰጣቸውን ሀገራዊ ተልዕኮ በላቀ ግዳጅ እንዲወጡ አሳስበዋል።
በስልጠናው አብላጫ ውጤት ላመጡ ተመራቂ አባላትና አሰልጣኞች የሽልማት አሰጣጥ ስነ-ስርአት ተካሂዷል።
በራሄል ገዛኸኝና በታገል አልማው





