የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ሃምሌ 12 ቀን 2017 ዓ.ም
የመከላከያ ኢንስፔክተር ጀኔራል ቢሮ ሃላፊ ሌተናል ጀኔራል ደሳለኝ ተሾመ በደቡብ ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል ተገኝተው ለሻለቃና ሻምበል አመራሮች ስልጠና ሰጥተዋል፡፡
ሌተናል ጀኔራል ደሳለኝ ተሾመ የተኪ አመራሮች ክህሎት በማሳደግ የሠራዊቱን የተኩስ አቅሙን በሥልጠና በማረጋገጥ ስልታዊ አቅሙን ማሣደግ፣ በእያንዳንዱ ግዳጅ ውጊያን መምራትና ማቀናጀት የሚችል ቀልጣፋ ውጤታማ በማድረግ በአጭር ጊዜና በአነስተኛ ኪሳራ ድልን የሚጎናፀፉ የነቃና የበቃ ሃይል በመገንባት ለሠራዊቱ አሸናፊነት አመራሩ የድል አስኳል ነው ብለዋል።
በሥልጠና ያገኛችሁትን እውቀት ተጠቅማችሁ ሃይል በመቆጠብ የዘላቂ ደህንነትን ለማስጠበቅና የብሄራዊ ጥቅምን ለማስከበር ብሎም የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ መሥራት የይጠበቅባችኋል ብለዋል።
የአካልና የአእምሮ ብስለትን በፅናት በመሰነቅ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መሰናክሎች ውስጥ በጀግንነት የሚያልፍ ውሳኔ በፍጥነትና በብቃት የመወሰን ችሎታ ያለው የጋራ ዓላማን ለማሳካት በመደበኛ በኢ-መደበኛ ጦርነት ውስጥ የመስራት አቅሙን በማዘመን በተፈለገው ልክ ግዳጁን በስኬት መወጣት የሚችል ሃይል መገንባቱንም ሌተናል ጄኔራል ደሳለኝ ተሾመ አንስተዋል፡፡
የሃገርን ሉአላዊነት ለመጠበቅ ፅኑ ሃገራዊ አቋም ያለው ወታደራዊ አመራርና አባላትን መገንባታችንን አጠናክረን በመቀጠል የለውጥ ተግባራትን ውጤት በማስጠበቅ ህገ-መንግስቱንና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን መጠበቅ እንደሚገባ አመላክተዋል።
ሃገሩን ከማንኛውም ጥቃት መመከት የሚችል የተደራጀ ሃይል በመገንባት የኢትዮጵያን ሠላምና ልማት ለማሣካት ምንጊዜም መሥራት ዝግጁ መሆን እንደሚጠበቅ ገልፀው ሠራዊታችን በአንድነት በሃገራዊ ስሜት በጋራ የተሰጠውን ተልዕኮ በቁርጠኝነት መፈፀም እንደሚገባውም አመላክተዋል።
ዘጋቢ በላይ ታደለ
ፎቶግራፍ ቦጋለ አጊሴ





