ኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ሃምሌ 10 ቀን 2017 ዓ.ም
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ወታደራዊ አማካሪና የተኩስ አመራር ሃላፊ ሌተናል ጀኔራል አለምሸት ደግፌ በደቡብ ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል ተገኝተው በስልጠና ላይ ለሚገኙ የሻለቃ እና የሻምበል አመራሮች የአመራር ትምህርት ሰጥተዋል፡፡
ሌተናል ጀኔራል አለምሸት ደግፌ ሠራዊታችን በስልታዊ ስልጠናዎች የተኩስ ችሎታውን በማሳደግ የተሰጠውን ተልዕኮ አጉልቶ በመፈፀም የተደራጀ ዕዝና ቁጥጥር በማድረግ ዝግጁነቱን በማጠናከር ከምንጊዜውም በላይ የውጊያ መርሆችን በመተግበር በታጠቀው ትጥቅ ጠላትን ተዋግቶ መደምሰስ የሚያስችል አቅም መፍጠሩን ገልፀዋል፡፡
እንደ ተቋም ጠንካራ ፅኑ ቆራጥ ሃይል በመገንባት ወታደራዊ ዝግጁነትን በስልጠና በማሳደግ በየጊዜው በማደራጀት ፈጣን ተነቃናቂ ሃይል ተቋማችን ለሚሰጠን ተልዕኮ በብቃት መወጣት የሚችል በአካል ብቃትና፣ በስነ- አዕምሮው የዳበረ፣ በስነ-ልቦናው የታነፀ፣ ሞራል ያለው ሃይል መገንባቱንም አንስተዋል፡፡
ሠራዊታችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውን በሃላፊነት መንፈስ በመተግበር እርስ በእርስ በመደጋገፍ ውጊያን የሚጨርስና በድል የሚወጣ በእቅድ የተሰጠውን ተልዕኮ በራሱ ተነሳሽነት ጨምሮ የሚሰራ ወቅታዊ ሁኔታዎችን የሚያነብ፣ የመወሰን ችሎታው ከፍተኛ የሆነ ፣ ሃይልን ማደራጀትና የማስተባበር ልምድ ያካበተ መሆኑንም ሌተናል ጄኔራል አለምሸት ተናግረዋል።
በሁኔታዎች ቀደምተኝነትን የሚያተርፍ ወጥ አሰራር የሚከተል ሆኖ ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር የሚራመድ ጠላትን መደምሰስ የሚችል አመራርና ተመሪዎችን የማፍራት ተግባር በሥልጠና ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባው የገለፁት ጄኔራል መኮንኑ ማሠልጠኛ ማዕከሉ ለሥልጠና እየሠጠ ያለው ከፍተኛ ትኩረትና የአሠልጠኞች የማሠልጠን ብቃት ለሠልጣኙ አቅም ወሳኝ ሚና እንዳለውም አመላክተዋል።





