የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ሰኔ 28 ቀን 2017 ዓ.ም
የምስራቅ ዕዝ በብር ሸለቆ መሰረታዊ ውትድርና ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ያሰለጠናቸውን አመራሮች በደማቅ ስነ-ስርዓት አስመርቋል፡፡
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተው በስልጠናው ብልጫ ላመጡ ክፍሎችና በስልጠናው አስተዋፅኦ ላበረከተው የምዕራብ ጎጃም ዞን ሽልማት ካበረከቱ በኋላ የሥራ መመሪያ የሠጡት የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል መሀመድ ተሰማ፦ የዕዙ ሠራዊት ባደረጋቸው ዉጊያዎች ጠላትን በማሽመድመድ ታላላቅ ድሎችን በማስመዝገብ የሀገራችንን ሉዓላዊነትና የህዝባችንን ሰላም ማሥጠበቅ ችሏል፣ እያስጠበቀም ይገኛል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያን የማፍረስ ተልዕኮ ተቀብሎ ፅንፈኛው ፍላጎቱን በሀይል ለማሳካት የከፈተብንን ጥቃት ተቋማችን ከፌደራልና ከክልል የፀጥታ ሀይሎች ጋር እንዲሁም ከሰላም ወዳዱ ህዝብ ጋር በመሆን ባደረጋቸው ውጊያዎች በሀገር ላይ መከፈል ያለበት ዋጋ ተከፍሎ አሁን ሀገራችንን ከብተናና ከመፍረስ ታድገናል ያሉት ሌተናል ጄኔራል መሀመድ ተሠማ ለዚህ መሳካት የሠራዊቱ አመራሮች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአንድ ብቁ አመራር ተግባር በሰላም ጊዜ ራሱንና የሚመራውን ሠራዊት አቅም በስልጠና መገንባት እና ወትሮ ዝግጁነቱን በማረጋገጥ የአሸናፊነት ስነ ልቦናውን መገንባት ነው ያሉት አዛዡ በሰላም ወቅት የተገነባውን አቅምና ብቃት ጠላትን ተዋግቶ በአነስተኛ ኪሳራ መደምሰስ በመሆኑ አሁን የተመረቃችሁ አመራሮችም እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ጀግንነታችሁን አጠናክራችሁ መቀጠል ይገባችኋል ሲሉ አሥገንዝበዋል፡፡
ቅጥረኛ ሀይሎችን በመምታት ስጋት ወደ ማይሆኑበት ደረጃ ላይ ብናደርስም የሀገራችንን ልማት የማይፈልጉ የውጭና የውስጥ ጠላቶች ስላሉን እየሰለጠን በመዋጋት ለቀጣይ ሀገራዊ ግዳጅ መዘጋጀት አለብን ብለዋል ሌተናል ጄኔራል መሀመድ ተሠማ፡፡
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የምስራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ
ሜጄር ጀኔራል ግዛው ኡማ፣ የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዕድሜአለም አንተነህ፣ የኮር አዛዦች ፣ የብር ሸለቆ መሰረታዊ ውትድርና ትምህርት ቤት አዛዥ እና ሌሎች የሠራዊቱ አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
ዘጋቢ ታደሰ ይሴ
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ድረ-ገፅ
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ዩቲዩብ
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ቴሌግራም
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ፌስቡክ
