የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ሚያዚያ 08 ቀን 2017 ዓ.ም
ውይይቱን የመሩት የሶማሌ ክልል ርዕሠ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ የአገራችን የምስራቁ ቦርደር ደህንነትን በማረጋገጥና የክልላችን ሰላምና ፀጥታ ፀንቶ እንዲቀጥል በማድረግ ረገድ መከላከያ ሠራዊታችንና የክልሉ ፀጥታ ሀይሎች እንደ አገር እንድንኮራ አድርገውናል ብለዋል።
ክልላችን ከለውጡ በኃላ ህብረተሰቡን በማሳተፍ በሰራቸው ስራዎችና የፀጥታ ሀይሎች የማጠናከር ተግባራት እንደ ክልል ተከስቶ የነበረውን ነውጥ በመቀልበስ አሁን የተገኘውን አስተማማኝ ሠላም ማምጣት ተችሏል ነው ያሉት።
አቶ ሙስጠፌ መሀመድ አገራችን የያዘችውን ፈጣን ዕድገት ለማደናቀፍ አልሸባብና የውስጥ ፀረ-ሰላም
ሀይሎች ተናበው የምስራቁን ቦርደር አደጋ ላይ እንዳይጥሉ የፀጥታ ሀይሉ በንቃት መከታተል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በመከላከያ ዘመቻ ዋና መምሪያ የሃይል ክትትልና ስምሪት መምሪያ ሃላፊ ሜጄር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው ኢትዮጵያን በምስራቁ ቦርደር ለመተንኮስ ባለፉት ጊዜያት አልሸባብ በርካታ ሙከራዎችን ያደረገ መሆኑን ጠቁመው ህብረተሰቡን ጨምሮ የመከላከያ ሠራዊትና የክልሉ ፀጥታ ሀይሎች የአገሪቱን ቦርደርም ሆነ ክልሉን ሳያስደፍሩ መቆየታቸውን አንስተዋል።
የምስራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ ለውጊያ ድጋፍ አገልግሎት ሜጄር ጄኔራል ፍቃዱ ፀጋዬ አንደኛው የዕዙ ተልዕኮ የምስራቁን ቦርደር ደህንነት ማረጋገጥና የአካባቢውን ሰላም መጠበቅ መሆኑን ተናግረው ሠራዊታችንም ለዚህ ተልዕኮ መሳካት በተጠንቀቅ የቆመና ፀረ-ሰላም ሀይሎችን ተከታትሎ እርምጃ በመውሰድ የግዳጅ ቀጠናው አስተማማኝ ሰላሙ እንዲቀጥል አድርጓል ብለዋል።
የሶማሌ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀኔራል አብዲ አሊ በበኩላቸው ፀጥታ ሃይላችን የክልሉን ሰላም ከመጠበቅ ባለፈ የምስራቁን ቦርደር በመዝጋትና በመጠበቅ ተደጋጋሚ የአልሸባብ ሙከራዎችን ማከሸፍ መቻሉን አሥረድተዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት 99 የአልሸባብ አባላትን በመደምሰስ ለጠላት ምስራቅ ኢትዮጵያ እንደማይቀመስ ያሳየና ከድምበር ባሻገር ከጀግናው መከላከያ ሠራዊት ጋር ግዳጆችን በመጋራት ድሎችን አስመዝግበናል ብለዋል።
ዘጋቢ ሳምሶን ባህሩ
ፎቶ ግራፍ ሳምሶን ባህሩ
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ዩቲዩብ
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ቴሌግራም
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ፌስቡክ
