118ኛው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቀን “የማትደፈር ሀገር የማይበገር ሠራዊት” በሚል መሪ ቃል በቢሾፍቱ ከተማ ሲከበር የመከላከያ ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሃመድ መልዕክት አሥተላልፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጥንካሬ ከሚዋደቁላት ጀግኖች የመነጨና ተለይቶም የማይታይ፤ እንዲሁም ውድ የሰራዊታችን አባላት ፀንተው እስካሉ ድረስ ሉዓላዊነታችን፣ አንድነታችንና ክብራችን እንደማይናወጥ የሚያስገነዝበን ነው ያሉት ክብርት ሚኒስትሯ ሁልጊዜም አንድ ህዝብ ማንነቱን በክብር የሚያስታውስባቸው ቀናት አሉት- የዛሬው ቀንም ከእነዚህ መገለጫዎች መካከል አንዱ ነው ብለዋል።

ይህ ቀን የጀግናው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊታችንን ክብርና ታላቅነት ይበልጥ ከፍ የምናደርግበት፣ ውድ የሰራዊታችን አባላት ለአገራቸው ለከፈሉት ክቡር መስዋዕትነት ያለንን ጥልቅ ምስጋና የምንገልፅበትና ፣ ለሀገራችን ጋሻ ሆነው በመቆም ላበረከቱት ፅኑ አገልግሎታቸው በፍፁም ቁርጠኝነት በሁሉም ፈተና እና ድል ከጎናቸው ለመቆም ያለንን ዘላቂ ፅናት የምናረጋግጥበትና ያለንን የማይናወጥ የቁርጠኝነት ቃል ኪዳንም የምናድስበት ቀን ነው ሲሉም ገልፀዋል፡፡
የመከላከያ ሰራዊታችን በየትውልዱ ፣የነፃነታችን የልብ ትርታና የጋራ ዕጣ ፈንታችን ፅኑ ጠባቂም ሆኖ መኖሩን በታሪክ ደጋግሞ አስመስክሯል፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የፀናችው ጋሻዎቿ ፈፅሞ ስላልተሸነፉና ስላልደከሙ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ለዘመናት በውስጥ ግጭቶች፣ በውጭ ወራሪዎች እንዲሁም በፖለቲካዊ ፈተናዎች ተግዳሮቶች ገጥመዋታል፤ ነገር ግን እንደ ሉዓላዊ ሀገር በአስደናቂ ሁኔታ ፀንታ የቆመችው በውድ የመከላከያ ሰራዊቷ ፅናትና ጀግንነት መሆኑንም ኢንጂነር አይሻ አሥገንዝበዋል፡፡
ኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶቿ መቼም የሚተኙላት አገር አይደለችም የተትረፈረፈ የተፈጥሮ ፀጋ፣ ለም መሬትና የውሃ ሃብት፣ ታሪካዊ ቅርሶችና ሌሎችም ፀጋዎቿ ሁሉ ኢትዮጵያ ሁሌም ዕድልና ተስፋ የሰፈነባት ሀገር ሆና እንድትኖር ቢያደርጋትም ጠላቶቿ ምንግዜም ከዚህ ፀጋዋ እንዳትጠቀም ሊያሳንሷት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም ዛሬም ይህ በገሃድ የሚታይ እውነታ ነው በማለት ገልፀዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን እየተተገበረ ባለው ሪፎርማችንም የመከላከያ ሰራዊታችንን ወደ ዘመናዊና ሙያዊ ተቋምነት በመቀየር የታላቋን ሀገራችንን ጥንካሬና ክብር የሚያንፀባርቅ ተቋም ለማድረግ ችለናል ያሉት ኢንጂነር አይሻ መሃመድ የመከላከያ መሠረተ ልማታችንን በማጎልበት እና የሰራዊታችንን ክህሎት፣ ዝግጁነት እና የመቋቋም አቅም በማዳበርም ብዙ ርቀት ተጉዘናል ብለዋል።
ዛሬ 118ኛውን የሠራዊት ቀን ስናከብር ለሀገራችን ዘብ ለቆሙት የሰራዊታችን አባላት ያለንን ልባዊ ቃል ኪዳን በማደስ ነው፡፡ ሁሌም መስዋዕትነታቸውን በማክበር ተልዕኳቸውን በመደገፍ፣ እንደ አንድ ህዝብ በአንድነት ቆመን እንነሳ በማለት ጥሪን ማስተላለፍ እፈልጋለሁ ሲሉ ኢንጂነር አይሻ መሃመድ መልዕክት አሥተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ ውብሸት ቸኮል
ፎቶግራፍ ተሰማ ኡርጌሳ
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ድረ-ገፅ
https://dfmc.mod.gov.et/
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ዩቲዩብ
https://youtube.com/@fdredefenseforce-9629?si=Av-sDKCopw1FfTW2
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ቴሌግራም
https://t.me/+E_EOiTY9eq85ODI0
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ፌስቡክ
https://www.facebook.com/fdredefense.official





