የመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ ለአራት ወራት ያሰለጠናቸውን የአጭር ኮርስ ተማሪዎች አስመርቋል።
በምረቃ መርሃ-ግብሩ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው ለተመራቂዎቹ የስራ መመሪያ የሰጡት የመከላከያ ትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ጄኔራል ይመር መኮነን መከላከያ አሁናዊ የአለምን የውጊያ አውድ ተረድተው የሚተነትኑና ሰራዊት የሚያዘጋጁ ከፍተኛ አመራሮችን እያፈራ መሆኑን ተናግረዋል ። የዛሬው ተመራቂዎችም የዚሁ አንድ ማሳያ እንደሆነም አስረድተዋል።

ተመራቂዎች ወደ ተመደባችሁበት አሃድ ስትመለሱ ባገኛችሁት ዕውቀት መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት ይጠበቅባችኋል ሲሉም አሳስበዋል።
የመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ዮሐንስ መኮነን በበኩላቸው ኮሌጁ የተቋሙን የዘመናዊ ሰራዊት ግንባታ ዕውን ለማድረግ ከአዲስ አበባ ዮኒቨርስቲ እና መሰል ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ጥራት ያለው ትምህርት እያስተማረ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ኮሌጁ ከተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች ውጭ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ወታደራዊ አመራሮችን እያስተማረ በማስመረቅ ተቀባይነትን ያገኘና ተመራጭ ኮሌጅ እንደሆነም አንስተዋል።
የኮሌጁ ትምህርትና ስልጠና ዲን ተወካይ ኮሎኔል ገብረእግዚአብሔር ኃይሉ፣ ኮሌጁ በተለያዩ የስልጠና ፕሮግራሞች አመራሮችን አሰልጥኖ ማሥመረቁን ገልፀው የዛሬ ተመራቂዎች በስትራቴጂክ ፣ በወታደራዊ አመራር፣ በጦርነት ጥናትና ትምህርት እንዲሁም በህብረት ዘመቻ ትምህርት በተግባርና ንድፈ ሀሳብ እንደተማሩ አስረድተዋል።

በመጨረሻም የ2018 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብርን በማስመልከት በኮሌጁ የችግኝ ተከላ ተደርጓል።
ዘጋቢ አባቱ ወልደማርያም
ፎቶግራፍ አበረ አየነው
