የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በአፍሪካ የአሜሪካ ዕዝ (አፍሪኮም) አዛዥ ጀነራል ዳግቪን አንደርሰን የተመራውን ልዑክ በቢሯቸው ተቀብለው በሁለቱ ሀገራት መካከል ባለው የመከላከያ ትብብር፣ በቀጠናዊ ደህንነት እና በጋራ የሚከናወኑ የወደፊት የትብብር መስኮች ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል።

በአፍሪካ የአሜሪካ ዕዝ (አፍሪኮም) አዛዥ ጀነራል ዳግቪን አንደርሰን ከኢትዮጵያ ጋር ያለው የመከላከያ ትብብር በተለያዩ ዘርፎች እየተጠናከረ መምጣቱን ገልጸው፣ ይህም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ የመከላከያ አጋርነትና የጋራ ቁርጠኝነት የሚያንጸባርቅ መሆኑን አስታውቀዋል።
በውይይቱ ወቅት የትብብር መስኮችን ማስፋት፣ በሶማሊያ አልሸባብንና አይኤስ አይኤስን ጨምሮ በሽብርተኝነት ላይ የሚደረገውን ትግል ማጠናከር እንዲሁም ወደፊት ያሉ የትብብር ዕድሎችን መለየት ዋና የውይይቱ አጀንዳዎች እንደነበሩ ጀነራል ዳግቪን አንደርሰን ገልጸዋል።
ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ኢትዮጵያ እያበረከተች ያለችውን አስተዋፅኦ ያደነቁት ጀነራል መኮንኑ፣ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ የአፍሪካ የሎጂስቲክስና የኮሙኒዩኬሽን ሲምፖዚየምን ማዘጋጀት መቻላቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የመከላከያ ትብብር የደረሰበትን ከፍተኛ ደረጃ የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሁለቱ ወዳጅ ሀገራት ግንኙነት ከጋራ ወታደራዊ ተልዕኮዎች ባሻገር ዘላቂና ዘመናዊ የመከላከያ አቅምን በመገንባት ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ በአህጉሪቱ ያሉ የደህንነት ተግዳሮቶችን በጋራ ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነትም እንደሚያሳይ ጠቁመዋል።
የጉብኝታቸው ዋና ዓላማ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ መከላከያ ሠራዊት ጋር በመተባበር የአፍሪካ የሎጂስቲክስና የኮሙኒኬሽን ሲምፖዚየምን ማካሄድ መሆኑን ገልጸው፣ ሲምፖዚየሙ ልምድ ለመለዋወጥ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዋወቅ፣ ከንግድ ዘርፉ ጋር ትብብርን ለማሳደግና የአፍሪካ የመከላከያ ተቋማትን አቅም ለማጠናከር ጠቃሚ መድረክ መሆኑን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ የአህጉሪቱን ሀገራት በአንድ መድረክ በማሰባሰብ የጋራ የደህንነት ችግሮችን ለመፍታት ያላትን የአመራር ሚና እያሳየች መሆኑን ገልጸዋል።
የመከላከያ የውጭ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክትሬት ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ በበኩላቸው፣ ውይይቱ ፍሬያማ እንደነበርና በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ወዳጅነትና የመከላከያ ትብብር የበለጠ የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።

በውይይቱ ላይ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋን ጨምሮ የሁለቱ አገራት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ ብዙአየሁ ተሾመ
ፎቶግራፍ ተሰማ ኡርጌሳ
