የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ክቡር ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን ስር እየተካሄዱ ያሉ የአዳማ ጋርመንትና ኢንዱስትሪ፣ የጋሻ የሠራዊቱ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ፕሮጀክት እና የመከላከያ ባጅና ሜዳሊያ ማምረቻ ፋብሪካን ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ወቅት የአዳማ ጋርመንት ኢንዱስትሪ ያስገነባውን አዲስ የማስፋፊያና የማሻሻያ ፕሮጀክት በይፋ መርቀው ከፍተዋል።
በጋሻ መኖሪያ ፕሮጀክት፣ በአዳማ ጋርመንት ኢንዱስትሪ እንዲሁም በመከላከያ ባጅና ሜዳሊያ ማምረቻ ፋብሪካ የተከናወኑ የልማት ስራዎችን የጎበኙት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የፋውንዴሽኑን አመራሮችና ሰራተኞች ላስመዘገቡት ውጤት አመስግነው፣ የተገኘው ለውጥ ሳያዘናጋቸው ለበለጠ ውጤት እንዲተጉ አሳስበዋል።

በቀጣይም የምርት ጥራትን በማሻሻል፣ የምርምርና የቴክኖሎጂ ልማትን በማስፋፋት፣ የዲጂታላይዜሽን ስራዎችን በማጠናከር፣ የግብዓት አቅርቦትን በራስ አቅም በማሳደግ በአፍሪካ ደረጃ ተወዳዳሪ ኢንዱስትሪ እንዲገነባ አቅጣጫ ሰጥተዋል።
“ሰራዊቱ መለኪያው ሀገሩ ነው” ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የመከላከያ ሰራዊት ፋውንዴሽን የተቋሙንና የሀገሪቱን ፍላጎት በማሳካት ያለውን ሚና ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባው አመላክተዋል።

በጉብኝቱ ላይ የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ሀይሉ ጀልዱን ጨምሮ የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አመራሮች እና የፋውንዴሽኑ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ ብዙአየሁ ተሾመ
ፎቶግራፍ ተሰማ ኡርጌሳ
