የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽንና ዓለም አቀፉ የሪፖርታጅ ፕሮፐርቲ ጋር በጋራ ለመስራትና በዘላቂ ጥቅም ላይ ያተኮረ የልማት ሥራ ለማከናወን የሚያስችል ስትራቴጂያዊ ስምምነት ተፈራረሙ።
በስምምነቱ ፊርማ ሥነ-ሥርዓት ላይ የመከላከያ ፋይናንስ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ማርታ ሉዊጂ በተገኙበት የተካሄደ ሲሆን፣ ስምምነቱ ለሀገራዊ ዕድገት፣ ለዘላቂ ልማትና ለሠራዊቱ ተጠቃሚነት የሚኖረው ሚና የጎላ መሆኑ ተገልጿል።

በዝግጅቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ወይዘሮ ማርታ ሉዊጂ የሁለቱ ተቋማት ትብብር ከግንባታ ባለፈ ለሀገሪቱ የከተማ ልማት፣ ለሥራ ፈጠራና ለቴክኖሎጂ ሽግግር አዲስ ዕድሎችን የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።
በሳር ቤት አካባቢ የሚገነባው ዘመናዊ የመኖሪያና የከተማ ልማት ፕሮጀክት ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ ግንባታ በማስገንባት ለከተማዋ ዕድገትና ለኢኮኖሚው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቱ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር፣ የዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂና ዕውቀት ሽግግርን ለማስፋፋት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ተብሏል።
የሪፖርታጅ ፕሮፐርቲ ሰብሳቢ አቶ አሪፍ አልኩሪ በበኩላቸው፣ ድርጅታቸው ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ከመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን ጋር በጋራ መስራት መጀመሩ የሚያስደስት እድል መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት አቅም ያላት ሀገር መሆኗን የጠቆሙት አቶ አሪፍ አልኩሪ ፣ ድርጅታቸው ያለውን ዓለም አቀፍ ልምድና የቴክኖሎጂ አቅም በመጠቀም ለሀገሪቱ ዕድገት የሚችለውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ቁርጠኛ መሆኑን አስረድተዋል።
በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል የተባለው ፕሮጀክት የትብብር፣ የዘላቂ ልማትና የብልጽግና መሠረት ይሆናልም ብለዋል።
ሪፖርታጅ ፕሮፐርቲ ከ28 በላይ በሆኑ ሀገራት የተሰማራ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ስምንቱ በአፍሪካ የሚገኙ መሆናቸው ተገልጿል።
በዝግጅቱ ላይ በኢትዮጵያ የዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ አምባሳደር አቶ አብደላ ሀሰንን ጨምሮ ከፍተኛ የሰራዊቱና የድርጅቱ አመራሮች፣ ባለሀብቶችና ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ ብዙአየሁ ተሾመ
ፎቶግራፍ ተሰማ ኡርጌሳ
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት
https://dfmc.mod.gov.et/
https://youtube.com/@fdredefenseforce-9629?si=Av-sDKCopw1FfTW2
https://t.me/+E_EOiTY9eq85ODI0
