የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ሰኔ 17 ቀን 2017 ዓ.ም
የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ክቡር ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የመከላከያ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል የህክምና አሠጣጥ ሂደቱን ተመልክተዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ የሪፈራል ሆስፒታሉን የእንግዳ ማረፊያም መርቀዋል። የእንግዳ ማረፊያው ሁሉንም ዓይነት የእንግዳ መቀበያ መሥፈርት ያሟላ 26 የመኝታ ክፍሎች ያሉት ነው።
የመከላከያ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል የህክምና አሠጣጥ ሂደቱን የተመለከቱት ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ሆስፒታሉ በህክምና መሣሪያዎች ቴክኖሎጅና በሙያተኛ ዘመናዊነትን በተከተለ አግባብ ዘምኖ የሪፈራል ሆስፒታል መሆን እንዲችል መከላከያ ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ ማድረጉን ገልፀዋል።
በአለማችን በጦር መሣሪያ፣ በህክምና መገልገያ መሣሪያ፣ በኢንዱስትሪ እና በሌሎች የቴክኖሎጅ ዘርፎች ሞዴል የሚሆኑ ሙያተኞች የሚፈልቁት ከውትድርናው ቤት ነው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ኢትዮጵያ በየጊዜው ሲገጥማት በነበረው ጦርነት ምክንያት ሞዴል ሳንሆን መቆየታችንን ገልፀው አሁን ላይ ግን በሁሉም ዘርፍ ዘመናዊነትን በተከተለ አግባብ ከቴክኖሎጅው ጋር መላመድና አብሮ ማደግ ይኖርብናል ብለዋል።
ሪፈራል ሆስፒታሉን በማዘመን ወደ ውጪ የሚሄዱ ታካሚዎች እዚሁ እንዲታከሙ የማድረጉ ጥረት ትልቅ ተስፋ ሰጪ በሆነ መንግድ ስኬታማ ሆኗል ለዚህም የ87 የሠራዊት አባላት የዳሌ አጥንት ቅየራ ሥራ በውጤት መሣካት ዋናው ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።
የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ የሆስፒታሉ ፅዳትና ውበት እጅግ በተለዬ መንገድ ሳቢ ለሥራ ምቹነት የሚፈጥር ሞዴል በሆነ አግባብ መሠራቱን አድንቀው የመከላከያ ጤና ዋና መምሪያ ኃላፊን ጨምሮ የመከላከያ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል አመራሮች ላደረጉት ያልተቆጠበ የሥራ ተነሳሽነት ምስጋና አቅርበዋል።
በጉብኝቱ ላይ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላን ጨምሮ ጄኔራል ጌታቸው ጉዲና ጄኔራል መኮንኖች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ ውብሸት ቸኮል
ፎቶግራፍ ተሠማ ኡርጌሳ
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ድረ-ገፅ
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ዩቲዩብ
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ቴሌግራም
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ፌስቡክ





